Psalms 97

የእግዚአብሔር ድል አድራጊነት

1 እግዚአብሔር ነገሠ፤ ምድር ደስ ይበላት፤
በሩቅ ያሉ የባሕር ጠረፎች ሐሤት ያድርጉ።
2ደመናና ጥቅጥቅ ያለ ጭጋግ በዙሪያው አለ፤
ጽድቅና ፍትሕ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።
3እሳት በፊቱ ይሄዳል፤
በዙሪያው ያሉትንም ጠላቶቹን ይፈጃል።
4መብረቁ ዓለምን አበራ፤
ምድርም አይታ ተንቀጠቀጠች።
5ተራሮች በእግዚአብሔር ፊት፣
በምድርም ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ።
6ሰማያት ጽድቁን ያውጃሉ፤
ሕዝቦችም ሁሉ ክብሩን ያያሉ።

7ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ፣
በጣዖታትም የሚመኩ ሁሉ ይፈሩ፤
እናንተ አማልክት ሁሉ፤ ለእርሱ ስገዱ።

8 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ፍርድህ፣
ጽዮን ሰምታ ደስ አላት፤
የይሁዳም ሴት ልጆች ሐሤት አደረጉ።
9 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል ነህና፤
ከአማልክትም ሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ያልህ ነህ።
10 እግዚአብሔርን የምትወድዱ ክፋትን ጥሉ፤
እርሱ የታማኞቹን ነፍስ ይጠብቃልና፤
ከዐመፀኞችም እጅ ይታደጋቸዋል።
11ብርሃን ለጻድቃን፣
ሐሤትም ልባቸው ለቀና ወጣ።
12እናንት ጻድቃን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤
ቅዱስ ስሙንም አመስግኑ።
Copyright information for AmhNASV